Back

ⓘ ሕይወት እምሻው- Hiwot Emishaw Alemayehu
                                     

ⓘ ሕይወት እምሻው- Hiwot Emishaw Alemayehu

ሕይወት እምሻው- Hiwot Emishaw

የዚህ ታሪክ አሰባሳቢ፣ ተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒኬሽን በስነ-ጽሁፍ፣ በስነ-ስእል፣ በፊልም ፣ በቴአትር፣ በሬድዮ ድራማ ፤ በማስታወቂያ ዘርፍ ፤ በሚድያ ዘርፍ ከ1990ዎቹ ጀምሮ አስተዋጽኦ ያበረከቱና አሁንም በስራ ላይ ያሉ ባለሙያዎችን ታሪክ በፌስ ቡክ ፤ በዊኪፒዲያ እንዲሁም በሌሎች የማህበራዊ ሚድያዎች እያስተዋወቀ እንዳለ ይታወቃል፡፡ ውድ ይህን ሀሳብ የምትደግፉ መስፈርቱን ያሟላሉ የምትሏቸው ሰዎች ጠቁሙን ፤ እርስዎም ታሪኬ መሰነድ አለበት ካሉ ይላኩልን፡፡ ከተቀመጠው መስፈርት አንጻር አይተን ታሪክዎን እናወጣለን፡፡ በ tewedajemedia gmail.com ግለ-ታሪክዎን ይላኩ፡፡ ጥቅምት 14 2014 የ1000 ሰዎች ታሪክ ሲሞላ ድንቅ ታሪካዊ ምረቃ ይኖራል፡፡ ታሪካቸው አሁን የሚሰራላቸው፤ ብዙዎቹ በወጣትነት አንዳንዶቹም በጉልምስና እድሜ ላይ የሚገኙ ሲሆኑ የዛሬ ጎልማሳ የነገ የሀገር ባለውለታ ነውና ታሪካቸውን እየሰነድን ለትውልድ እናስቀምጣለን፡፡ ለወደፊቱም ምርምር ለሚያደርጉ እና ወይም የስራ ፕሮጀክቶቻቸውን ለሚደግፉ ሰዎች ይጠቅማል ብለን እናምናለን፡፡ በ7 ዘርፎች ትልቅ ስራ ሰርተዋል ብለን ያመንባቸውን ሰዎች ታሪክ እናቀርባለን፡፡ ይህ የማስተዋወቅ ስራ ውድድር ሳይሆን በሙያው የተለየ ሚና ያበረከተ ማንኛውም ሰው ታሪኩ የሚሰነድበት ነው፡፡ ጋን በጠጠር ይደገፋል እንዲሉ ሙያቸውን በመደገፍ የራሳቸውን አሻራ ያኖሩ ሰዎች ታሪካቸው ይዘከራል፡፡ አሁን ድርሰትና ወጎችና ስነ-ጽሁፍ ዘርፍ ታሪኳ የሚሰነደው ህይወት እምሻው አለማየሁ ናት፡፡

ትውልድ ልጅነትና ትምህርት

ሕይወት እምሻው የተወለደችው በ1974 ሰሜን ሸዋ ዞን ልዩ ስሟ መሀል ሜዳ በምትባል ስፍራ ነው፡፡ ነፍስ ሳታውቅ ከአባቷ ከአቶ እምሻው ዓለማየሁና ከእናቷ ወ/ሮ ኤልሳቤጥ ነጋሳ ጋር ወደ አዲስ አበባ የመጣችው ሕይወት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን በአግአዝያን ቁጥር አንድ፣ እንዲሁም በየካ ምስራቅ ጮራ ቢትወደድ ተከታትላለች፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን በኮከበ- ጽብኃ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ያጠናቀቀች ሲሆን፣ የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስድስት ኪሎ ካምፓስ ተከታትላለች፡፡

ዩኒቨርሲቲ

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ስትቀላቀል በወቅቱ አባቷ ሕግ እንድትማር አጥብቀው ቢወተውቷትም፣ ፍላጎቷ ፖለቲካ ሳይንስ መማር ስለነበር የሕግ ትምህርቱን አሻፈረኝ ያለቸው ሕይወት፣ በዩኒቨርሲቲ ቆይታዋ የመጀመሪያ ዲግሪዋን በፖለቲካ ሳይንስ ተከታትላ በከፍተኛ ውጤት አጠናቃለች፡፡ ያለምንም ፋታ ትምህርቷን በመቀጠልም የሁለተኛ ዲግሪዋን ከዚሁ የትምህርት ክፍል በዓለማቀፍ ግንኙነት አግኝታለች፡፡

ወደ ስራ አለም- በሕጻናት አድን ድርጅት Save the Children

የመጀመሪያ መደበኛ ሥራዋን በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ጉባኤ የጀመረቸው ሕይወት፣ በተለያዩ የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ውስጥ በኮሙኒኬሽንና አድቮኬሲ ባለሙያነትና ኃላፊነት ያገለገለች ሲሆን፣ አሁንም በሕጻናት አድን ድርጅት Save the Children ዓለም አቀፍ ተቋም የምስራቅና የደቡብ አፍሪካ ቀጠና የአድቮኬሲና ፖሊሲ ኃላፊ ሆና እያገለገለች ትገኛለች፡፡ ሕይወት የአኩዩመን ኢስት አፍሪካ ሊደርሺፕ ፕሮግራም የ2017 ፌሎው Acumen East Africa Leadership Program 2017 fellow ናት፡፡

የኪነ-ጥበብ ዝንባሌ

የሕይወት የሥነ-ጽሑፍ ሕይወት የጀመረው በኮከበ- ጽብኃ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚኒ ሚዲያ አስተባባሪነትና ጋዜጠኝነት ሲሆን፣ በወቅቱ ትልቁ ህልሟ ጋዜጠኛነት የነበረ ቢሆንም፣ የከፍተኛ ትምህርት የመቀጠል እድሉን ስታገኝ ፖለቲካ ሳይንስ ትምህርት ዝንባሌዋን አሸንፎታል፡፡ ሆኖም ሕይወት በዩኒቨርሲቲ ቆይታዋ፤ በስድስት ኪሎ ግቢ በባህል ማዕከል በተማሪዎች ይካሄድ በነበረው የሥነ-ጽሑፍ ምሽት ላይ በመሳተፍና መጣጥፎች በማቅረብ ከጥበብ ሳትርቅ ለመቆየት ሞክራለች፡፡ ከስድስት ኪሎ ግቢ ትምህርቷን አጠናቃ ከወጣች በኋላ በመደበኛ ሥራና የሥራ ዓለም ተውጣ ለዓመታት ከጽሑፍ ርቃ የቆየችው ሕይወት፣ ዳግም ወደ ሥነ-ጽሑፉ ዓለም የመለሳት ፌስቡክ ነበር፡፡

በግል የፌስ ቡክ ገጿ ላይ መጣጥፍ መጫር የጀመረቸው ሕይወት በኋላም ነቆራና ሌሎችም ወጎች ከሕይወት እምሻው ጋር በሚል በከፈተችው ገጽ የትርፍ ጊዜ ጸሐፊ በመሆን፤ ወጎቿን፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ሂሶቿን ለተከታዮችዋ እያስነበበች ትገኛለች፡፡

ሕይወት በ2007 ባርቾን በ 2010 ፍቅፋቂን ሁለቱም የወጎችና ልብወለዶች ስብስብ እንዲሁም በ2011 ማታ የተሰኘውን የአጭር ልብ-ወለዶች ስብስብ መጽሐፎችዋን ለአንባብያን አበርክታለች፡፡

በግልና" ነቆራና ሌሎችም ወጎች ከሕይወት እምሻው ጋር” በሚሉት የፌስቡክ ገጾችዋ ከ170 ሺህ በላይ ተከታዮች ያሏት ሕይወት እምሻው፣ ከፍተኛ ተነባቢነትን ያተረፉ ባርቾ፣ ፍቅፋቂና ማታ የተሰኙ ሶስት መጽሐፎችን ለንባብ ያበቃች ጸሐፊ ናት፡፡ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጾቿና በመጽሐፍዎችዋ የሷን ዘመን ትውልድ ፈተና፣ ዕድል፣ ምኞትና ሕልም በዘመኑ ያላቸውን ቦታና ሕይወታቸውን፤ የፍቅርና የመለያየት ጉዳዮችን በሚገባ የተነተነችና ዘመኗን ከታሪክ ሰነድ ባልተናነሰ መዝግባ ያኖረች የዘመኗ ጸሐፊ ናት፡፡ ሕይወት እምሻው ባለትዳር ናት፡፡  

Users also searched:

...